Home Entertainment News ቦክሰኛው መሃመድ አሊ የሳላቸው ስዕሎች 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተሸጡ

ቦክሰኛው መሃመድ አሊ የሳላቸው ስዕሎች 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተሸጡ

by sam

ቦክሰኛው መሃመድ አሊ የሳላቸው ስዕሎች 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተሸጡ።

በኒውዮርክ ውስጥ በቦንሃም ጨረታ ድርጅት አማካኝነት 26 ያህል የሳላቸው የጥበብ ስራዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር።

በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠበቁት ስራዎች መካከል ‘ስቲንግ ላይክ ኤ ቢ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ስዕል በ425 ሺህ ዶላር የተሸጠ ሲሆን ይህም ከተገመተው አስር እጥፍ ነው።

አለም ካፈሯት ከታላላቅ አትሌቶች አንዱ የሆነው መሃመድ አሊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ገጣሚ በመሆኑ የሚወደስ ሲሆን ስለ ስዕል ስራው ግን ብዙ አይታወቅም።

የጨረታው ድርጅት መሃመድ ህይወቱን በሙሉ እየሳለ ነው ያሳለፈው በማለት ከጠቆመ በኋላ በሙያው አርቲስት በሆነው በአባቱ እየተበረታታ እና በመጨረሻም ስፖርተኛውና አርቲስት ከሆነው ሌሮይ ኒማን ትምህርቶችን ወስዷል ብሏል።

“መሐመድ አሊ ትውልድን የገለጸ የባህል ማማ ነበር። የሥነጥበብ ሥራው ለልቡ ቅርብ የሆኑትን ቦክስ፣ ሲቪል መብቶች፣ ሃይማኖት፣ የዓለም ሰላም እና ሰብዓዊነት የሚሉ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው” በማለት የጨረታው ድርጅት ቦንሃምስ የባህል ዳይሬክተር ሄለን አዳል ከሽያጩ በፊት ተናግረዋል።

ሥራዎቹ በኪነ ጥበብ ሰብሳቢው እና በጓደኛው ሮድኒ ሂልተን ብራውን ለጨረታ የቀረቡ ሲሆን መሃመድ በአውሮፓውያኑ በ1977 በቦስተን ውስጥ ካደረገው ፍልሚያ በኋላ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ሥዕሎቹን እንደሳለለት ተናግሯል።

አጠቃላይ የሽያጭ ዋጋው 945 ሺህ 524 ዶላር ሲሆን ከተጠበቀውም ሶስት እጥፍ ነው።

‘ስቲንግ ላይክ ኤ ቢ’ የተሳለው በአውሮፓውያኑ 1978 ሚሲሲፒ ውስጥ ሲሆን የመሃመድ አሊ ግጥምን በብቸኝነት ያካተተ ነው በማለት ቦንሃምስ አስፍሯል።

“እንደ ቢራቢሮ እየበረረ እንደ ንብ ይናደፍ ነበር። እውነት ነው! ብልህ ከሆንህ እንደ እኔ ሩጥ” ይል ነበር።

መሃመድ አሊ አብዛኛውን ጊዜ የቦክስ ዘይቤውን እንደ ቢራቢሮ እየበረረ እንደ ንብ የሚናደፍ በሚል ነበር የሚገልጸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአውሮፓውያኑ 1979 በቀይ ፣ ነጭ እና ሰማያዊ የተሳለውና “አሜሪካ እወድሻለሁ” የሚል ፅሁፍ ያለበት ስዕል በ150 ሺህ ዶላር የተሸጠ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1967 እስልምናን ከክርስትና ጋር በማነጻጸር የሳለው ስዕል ደግሞ 24 ሺህ 000 ዶላር መሸጡን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

መሃመድ አሊ በፓርኪንሰን በሽታ ሲሰቃይ ቆይቶ በአውሮፓውያኑ 2016 በ74 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

Leave a Comment

Related Posts

en_USEnglish