የደች ተወላጁ ድንቅ ሰዓሊ ቪንሰንት ቫን ጐግ ስዕል፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተብሎ ከተዘጋ ሙዚየም ውስጥ ለሊቱን ስርቆት እንደተፈፀመበት ሰኞ ዕለት ፖሊስ እና ሙዚየሙ ገልፀዋል።
በአምስተርዳም በስተምስራቅ የሚገኘው የሲንገር ላረን ሙዚየም እንደሚለው ከሆነ፣ “ዘ ፓርሶኔጅ ጋርደን አት ኑነን ኢን ስፕሪንግ 1884” ተብሎ የሚጠራው በደች ተወላጁ ሰዓሊ የተሰራው ስዕል ሰኞ እለት ከንጋት በፊት ተወስዷል። የዚያን እለት ተሲዓት በኋላ ከሙዚየሙ በስተውጪ ለቆመ ሰው የሚታይ ነገር ቢኖር በሙዚየሙ የፊት ለፊት መስታወት መካከል የሚገኘውን የተሰበረ በር የሸፈነ ትልቅ ነጭ ፓኔል ብቻ ነበር።
የሙዚየሙ ዋና ዳይሬክተር ኤቨርት ቫን ኦስ እንደተናገሩት፣ በአሜሪካዊያኑ ባልና ሚስት ዊሊያም እና አና ሲንገር የስዕሎች ስብስብን የያዘው ተቋም በተፈፀመው ስርቆት “ተቆጥቷል፣ ተደናግጣል፣ አዝኗልም” ብለዋል።
ግሮኒንገን በተሰኘችው ደቡባዊዋ የደች ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የግሮኒንገን ሙዚየም በውሰት የተገኘው ይህ ድንቅ የስዕል ሥራ ዋጋው እስካሁን በውል አልታወቀም። የቫን ጐግ የስዕል ስራዎች፣ ከስንት አንድ ጊዜ ለሽያጭ በሚቀርቡበት ወቅት፣ በጨረታቸው ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያስገባሉ።