Home Entertainment News የግዙፉ መኪና አምራች ግንባታ በእባቦችና በእንሽላሊቶች ምክንያት ተቋረጠ

የግዙፉ መኪና አምራች ግንባታ በእባቦችና በእንሽላሊቶች ምክንያት ተቋረጠ

by sam

ግዙፉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪናዎች አምራች ኩባንያ ቴስላ በጀርመን ለመገንባት ያሰበው ፋብሪካ በእባቦችና በእንሽላሊቶች ምክንያት ለጊዜው እንዲቆም መገደዱ ተሰምቷል።

የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ በመዲናዋ በርሊን አቅራቢያ በአውሮፓ የመጀመሪያው ነው የተባለውን የመኪና እና የባትሪ ማምረቻ ለመገንባት የደን ምንጣሮ ስራውን በማከናወን ላይ ነበር።

ነገር ግን አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ይህ ምንጣሮ እባብ እና እንሽላሊት ዝርያዎችን ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ይከራከራሉ።

ይህን ተከትሎም በፍራንክፈርት የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ምርመራዎች እስከሚከናወኑና ደህንነቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ የደን ምንጣሮ ስራው ለጊዜው እንዲቆም ትእዛዝ አስተላልፏል።

ቴስላ እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ እና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ማህበር የሚባል ድርጅት ጋር ከገባበት ክስ ሂደት ጋር እንዳይጋጭበት በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች እንደሚሉት የቴስላ ደን ምንጣሮ ስራ በአሸዋ ውስጥ የሚኖሩ የእንሽላሊት እና እባቦችን ሕይወት በእጅጉ ይጎዳል። እነዚህ ተሳቢ እንስሳት ደግሞ በአገሪቱ ጥበቃ ከሚደረግላቸው እንስሳት መካካል ናቸው ተብሏል።

”ግዙፉ ቴስላም እንኳን ቢሆን እራሱን ከሕግ በላይ ማድረግ አይችልም፤ የለበትምም” ሲሉ ተደምጠዋል ‘ግሪን ሊግ’ የተባለው የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ዋና ሐሀፊ ሄይንዝ ማስቸር።

የቴስላ መስራችና ዋና ኃላፊ ኤለን መስክ በያዝነው ህዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ ድርጅቱ በአውሮፓ የመጀመሪያውን ፋብሪካ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑን ይፋ ሲያደርጉ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2021 ላይ ወደ ስራ ለመግባት መታቀዱን ገልጸው ነበር።

በዓመትም 500 ሺ መኪኖችን ለማምረት እቅድ ተይዞ ነበር።

Leave a Comment

Related Posts

en_USEnglish