ቻይና ከጨረቃ ላይ የአለትና የአፈር ናሙናዎችን እንዲያመጣ ወደ ጨረቃ ያለከችው መንኩራኩር ተልዕኮውን በስኬት ጨርሶ ወደ ምድር መመለሱ ተነገረ።
‘ቻንግ ኢ-5’ የሚል መጠሪያ የተሰጠው መንኩራኩር ሕዳር 24 ነበር ወደ ጨረቃ ጉዞውን ያደረገው።
ለመጨረሻ ጊዜ ሶቪየት ሕብረት ነበረች ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪ ለማምጣት መንኩራኩር ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ጨረቃ የላከችው።
ስኬታማውን ተልዕኮ ተከትሎም ቻይና ከአሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረት በመቀጠል ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪ ማምጣት የቻለች ሶስተኛዋ አገር መሆን ችላለች።
ቻይና ይህ ጉዞ በድል መጠናቀቁ ከሚያስገኝላት ሳይንሳዊ ጥቅም በተጨማሪ በሕዋ ሳይንስ ምርምር የደረሰችበትን ምጥቀት ለተቀረው ዓለም ለማሳየት ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥርላት እንደሆነ ተገልጿል።
ከሕዋ የተመለሰው መንኩራኩር ምድር ሲደርስ በርካታ ባለሙያዎች ተቀብለውታል።
ወደ ጨረቃ ተልኮ የነበረው መሳሪያ ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪና የአፈር ቅንጣት ይዞ እንደሚመለስ የሚጠበቅ ሲሆን ምን ያክል ናሙና ይዞ ስለመመለሱ ግን የተባለ ነገር የለም። ነገር ግን ከ2 እስከ 4 ኪሎግራም ሊመዝን እንደሚችል ተጠቁሟል።
ወደ ጨረቃ የተላከው ቻንግ-5 የተባለው መንኩራኩር በጥንታዊ የቻይና ጨረቃ አማልክት የተሰየመ ነው።
ከጨረቃ የሚመጣው አለትና አፈር እስካሁን በሰው ልጅ ተጎብኝቶ ከማያውቅ የጨረቃ ክፍል እንደሆነም ተገልጿል።