ዛሬ ምሽት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ጣሊያን እንግሊዝን በመለያ ምት በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆን ችላለች::
ለንደን በሚገኘው ግዙፉ የዌምብሌይ ስታዲየም በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን በመለያ ምት ነው 3ለ2 ያሸነፈው::
የሁለቱ ቡድኖች መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ እኩል የተጠናቀቀ ሲሆን ለእንግሊዝ ሉክ ሾው እንዲሁም ለጣሊያን ሊዮናርዶ ቦኑቺ አስቆጥረዋል::
ሉክ ሾው ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ለእንግሊዝ ያስቆጠራት ጎል በአውሮፖ ዋንጫ ታሪክ ፈጣኗ ጎል በመባል ተመዝግባለች::
በውድድሩ ባሳየችው ድንቅ የጨዋታ አቀራረብ የዘንድሮውን ውድድር የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረችው ጣሊያን የአውሮፓ ዋንጫን በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ማሳካት ችላለች::
ጣሊያን በዚህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ያሸነፈችው እአአ በ1968 ነበር::
በሜዳው የተጫወተው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ለአውሮፓ ዋንጫ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን በ60ሺህ ደጋፊ ፊት ተጫውቶ ዋንጫ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል::
እንግሊዝ እአአ 1966 ካሸነፈችው የአለም ዋንጫ ውጪ ምንም ውድድር ላይ ሳይሳካላት 55 አመታት መቆጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ::
የጣሊያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነው ጂያን ሉጂ ዶናሩማ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሲሆን ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና የቼክ ሪፕብሊኩ አጥቂ ፓትሪክ ሺክ ደግሞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ተጋርተዋል::